በኢፌዴሪ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴርና በድሬዳዋ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ መካከል የ2019 በጀት ዓመት የዘርፉን እቅድ በቅንጅት ለመፈጸም የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ተፈርሟል።

ስምምነቱ የከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ሥራዎችን በተቀናጀ አካሄድ ለመፈጸም ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ቢሮው የዘርፉን የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ በጋራ በመያዝ ለመፈጸም፣ በሥራ አፈጻጸም ላይ የጋራ አቅጣጫ ለመከተልና የሚከሰቱ የአፈጻጸም ችግሮችን በቅንጅት ለመፍታት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

በስምምነቱ መሠረት የሁለቱ ተቋማት ሥራዎች በቅንጅት፣ በትብብርና በመናበብ እንዲመሩ ትኩረት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን በመወከል ከቢሮው ጋር የተፈራረሙ ባለሙያዎች ገልጸዋል።

በተለይም በመሬት አስተዳደር፣ በመሬት አገልግሎት አሰጣጥና በዘርፉ የሚከናወኑ ሥራዎች ላይ የተቀናጀ አሠራር በመፍጠር ለከተማ ነዋሪዎች ፈጣን፣ ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት ለማቅረብ የሚያግዝ ሥርዓት ለመዘርጋት እንደሚያግዝ ጨምረው ገልጸዋል።

የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮን በመወከል የጋራ ስምምነት ሰነዱን የፈረሙት ምክትል የቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴን ጌዲ በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና የድሬዳዋ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የተፈረመውን ስምምነት በተግባር በማስፈጸም የዘርፉን ተልዕኮዎች በተሳካ ሁኔታ ለማሳካትና ለከተማ ነዋሪዎች የሚሰጠውን የመሬት አገልግሎት በተሻለ ደረጃ ለማድረስ የጋራ ጥረታቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።

በማጠቃለያውም የሁለቱ ተቋማት የሥራ አመራርና ባለሙያዎች የሚኖራቸውን የመረጃ ልውውጥና የሙያ ትብብር በማጠናከር የዘርፉ ሥራዎች በተመሳሳይ አቅጣጫና በጋራ እቅድ እንዲመሩ ለማድረግ እንደሚያግዝ ተመላክቷል።

የስምምነት ሰነዱ መፈረሙን ተከትሎ የ2019 በጀት ዓመት የዘርፉ ዕቅዶች በተቀናጀ አሠራር እንዲፈጸሙ፣ የሥራ አፈጻጸም ተጠያቂነት እንዲጠናከርና የተገልጋዩ ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑ ተገልጿል።